እግዚአብሔር ወልድ ከስላሴ መካከል ፍፁም አምላክ ፍፁም ሰው የሆነው እየሱስ ክርስቶስ ነው። ዮሐ1:3 "በመጀመሪያው ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፥ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ። ይህ በመጀመሪያው በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ።ሁሉ በእርሱ ሆነ፥ ከሆነውም አንዳች ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም።" እዚህ ላይ ዮሀንስ " ቃል" የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ከመጀመርያውም ከእግዚአብሔር አብ ጋር እንደነበር ይገልጣል። ዮሐ 1:34 “እኔም አይቻለሁ እርሱም የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ መስክሬአለሁ።” ዮሐ 8:19 “እንግዲህ፦ አባትህ ወዴት ነው? አሉት። ኢየሱስ መልሶ፦ እኔንም ወይም አባቴንም አታውቁም፤ እኔንስ ብታውቁኝ አባቴን ደግሞ ባወቃችሁ ነበር አላቸው።” * ወልድን የማያውቅ አብን አያውቅም *የዘላለም ህይወት የሚሰጠው ወልድ ነው።ፍጡር ቢሆን ኖሮ አይችልም ነበር ፈጣሪ ስለሆነ ግን ህይወትን መስጠት ይችላል ዮሐ 20:31 “ነገር ግን ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ ታምኑ ዘንድ፥ አምናችሁም በስሙ ሕይወት ይሆንላችሁ ዘንድ ይህ ተጽፎአል።” እየሱስን መስማት ህይወት ነው። እርሱ ስልጣን ቢኖረውም የአባቱን ፈቃድ ለመፈፀም ፍፁም አምላክ ሆኖ ሳለ ፍፁም ሰው ሆነ።የአምላክነት ባህሪውን ይዞ ሰው ሆነ።በአንድ የእርሱ አካል ሁለት ያልተቀላቀሉ ባህሪያት ይዞ በምድር ላይ ተመላለሰ:: የወልድ የስራ ድርሻዎች *በስሙ ላሙኑት ህይወትን ይሰጣል ዮሐ5:21 “አብ ሙታንን እንደሚያነሣ ሕይወትም እንደሚሰጣቸው፥ እንዲሁ ወልድ ደግሞ ለሚወዳቸው ሕይወትን ይሰጣቸዋል።” * ስልጣን ሁሉ የሱ ነው። በራሱ ላይ መለኮታዊ ስልጣን አለው።አሳልፎ ለመስጠት ሆነ ለመውሰድ ስልጣን አለው። ዮሐ 10:18 “እኔ በፈቃዴ አኖራታለሁ እንጂ ከእኔ ማንም አይወስዳትም። ላኖራት ሥልጣን አለኝ ደግሞም ላነሣት ሥልጣን አለኝ ይህችን ትእዛዝ ከአባቴ ተቀበልሁ።” ዮሐ 16: 15 “ለአብ ያለው ሁሉ የእኔ ነው፤ ስለዚህ፦ ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋል አልሁ።” ዕብራውያን 1፥3 “እርሱም ( እየሱስ) የክብሩ መንጸባረቅና የባሕርዩ ምሳሌ ሆኖ፥ ሁሉን በስልጣኑ ቃል እየደገፈ፥ ኃጢአታችንን በራሱ ካነጻ በኋላ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ፤” የክርስቶስ ባህሪያት 1. ሁሉን ቻይ ነው ማቴ 14:19 እየሱስ አምስት ሺ ሰዎችን በታምር መገበ ዮሐ 2 ውሃውን ወደ ወይን ቀየረ መንፈስ ቅዱስ ከመውረዱ በፊት የተደረጉት ታምራት ሁሉ የክርስቶስን ፍፁም አምላክነት ፣የእርሱን ክብር አጉልተው የሚያሳዩ ነበሩ። ዮሐ 2:11 “ኢየሱስ ይህን የምልክቶች መጀመሪያ በገሊላ ቃና አደረገ፤ ክብሩንም ገለጠ፥ ደቀ መዛሙርቱም በእርሱ አመኑ።” 2. ዘልአለማዊ ነው ራእይ 22:13 “አልፋና ዖሜጋ፥ ፊተኛውና ኋለኛው፥ መጀመሪያውና መጨረሻው እኔ ነኝ።” 3. ሁሉን አዋቂ ነው ዮሐ 6:64 “ነገር ግን ከእናንተ የማያምኑ አሉ አለ:: ኢየሱስ የማያምኑት እነማን እንደ ሆኑ አሳልፎ የሚሰጠውም ማን እንደ ሆነ ከመጀመሪያ ያውቅ ነበርና።” ዮሐ 2:25 “ነገር ግን ኢየሱስ ሰዎችን ሁሉ ያውቅ ነበር፤ ስለ ሰውም ማንም ሊመሰክር አያስፈልገውም ነበርና አይተማመናቸውም ነበር፤ ራሱ በሰው ያለውን ያውቅ ነበርና።” 4. በሁሉም ስፍራ አለ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት በሁሉም ቦታ ይገኛል 5. የማይጠፋ የማይሞት ነው 1ጢሞ6:16 “እርሱ ብቻ የማይሞት ነው፤ ማንም ሊቀርበው በማይችል ብርሃን ይኖራል፤ አንድ ሰው እንኳ አላየውም ሊያይም አይቻለውም፤ ለእርሱ ክብርና የዘላለም ኃይል ይሁን፤ አሜን።” ዕብ 7: 15_16 “በማያልፍም ሕይወት ኃይል እንጂ በሥጋ ትእዛዝ ሕግ ሳይሆን ሌላ ካህን በመልከ ጼዴቅ ምሳሌ ቢነሳ፥ ይህ እጅግ አብልጦ የሚገለጥ ነው።” 6. ስግደትና አምልኮ የተገባው ነው ራዕይ 19:10 “ልሰግድለትም በእግሩ ፊት ተደፋሁ። እርሱም፦ እንዳታደርገው ተጠንቀቅ፤ ከአንተ ጋር የኢየሱስም ምስክር ካላቸው ከወንድሞችህ ጋር አብሬ ባሪያ ነኝ፤ ለእግዚአብሔር ስገድ፤ የኢየሱስ ምስክር የትንቢት መንፈስ ነውና አለኝ።” እየሱስ ፍጹም አምላክ ቢሆንም ፍፁም ሰውም ነው:: የእግዚአብሔርን ሀሳብ ለመፈፀም ሰው መሆን ግድ ነበር። ሰው ካልሆነ በኛ ቦታ ሆኖ መሞት አይችልም ነበር። ዕብ 2:14-15 “እንግዲህ ልጆቹ በሥጋና በደም ስለሚካፈሉ፥ እርሱ ደግሞ በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን በሞት እንዲሽር፥ ይኸውም ዲያብሎስ ነው፥ በሕይወታቸውም ሁሉ ስለ ሞት ፍርሃት በባርነት ይታሰሩ የነበሩትን ሁሉ ነጻ እንዲያወጣ፥ በሥጋና በደም እንዲሁ ተካፈለ።” ሰው ሆኖ በመስቀል ስለሞተ ክብር እና ህይወት ሆነልን። ሰው የሚለው ቃል እንደኔ እና እንደሌሎች በምድር የተመላለሰ ነፍስ፣ስጋ ና መንፈስ ያለው ነው። ፍፁም ሰው ስንል ከ2000 አመት በፊት በመንፈስ ከማርያም ተፀንሶ የተወለደ ማለታችን ነው። ማቴዎስ 1፥18 “የኢየሱስ ክርስቶስም ልደት እንዲህ ነበረ። እናቱ ማርያም ለዮሴፍ በታጨች ጊዜ ሳይገናኙ ከመንፈስ ቅዱስ ፀንሳ ተገኘች።” ይህ ነገር እንዴት እንደሆነ ለማወቅ፣ወይም ለመመራመር ከባድ ነው ምክንያቱም የእግዚአብሔር ስራ በሰው አይምሮ አይገለፅም።ቃሉም በመክብብ 11:5 ላይ እንደሚለው፧ “የነፋስ መንገድ እንዴት እንደ ሆነች አጥንትም በእርጉዝ ሆድ እንዴት እንድትዋደድ እንደማታውቅ፥ እንዲሁም ሁሉን የሚሠራውን የእግዚአብሔርን ሥራ አታውቅም።” የእየሱስ ክርስቶስ የዘር ሀረግ በማቴዎስ 1:1_17 እና በሉቃስ 3:23 _38 ላይ የተፃፈልን ሲሆን ማቴዎስ የፃፈልን በአይሁዶች ወግና ስርዓት ነው።የጀመረው ከአብርሃም ነው ከዛም ዬሴፍን አስገብቶታል።በአይሁድ ስርዓት ዘር የሚቆጠረው በአባት ነው፣ዬሴፍ ደሞ የእየሱስ ህጋዊ አባት ነው ፣የቤተሰቡም ሀላፊ ነበር።በዚህ ምክንያት እንጂ ከእርሱ ዘር ስለወጣ አይደለም ። ሉቃስ ደሞ እርሱ ራሱ አህዛብ ስለነበር የፃፈውም ከአህዛብ ወደ ክርስትና ለመጡት ሰዎች ነው።እርሱ የጀመረው ከዬሴፍ ነው፡ ወደ ኋላ ቆጥሮ አብርሃምን አልፎ ወደ አዳም ደረሰ። ዳዊት ዘር ላይ ሲደርስ የሁለቱ አፃፃፍ ይለያያል።ዳዊት ብዙ ልጆች ስለነበሩት ማቴዎስ የወሰደው የሰለሞንን ዘር (አይሁድ ስለነበረ) ፣ሉቃስ ደሞ የናታንን መስመር መርጦ ነው። ከማርያም ወደ እየሱስ አዳማዊ ሀጥያት አልተላለፈም፣ መንፈስ ቅዱስ ስለፀለላት እና ደግሞ የፀነሰችው በመንፈስ ቅዱስ ሃይል ስለሆነ:: ክርስቶስ ከሀጢያት በስተቀር ሙሉ በሙሉ የሰው ባህሪ አለው። ሮሜ 1:3 “ይህም ወንጌል በሥጋ ከዳዊት ዘር ስለ ተወለደ እንደ ቅድስና መንፈስ ግን ከሙታን መነሣት የተነሣ በኃይል የእግዚአብሔር ልጅ ሆኖ ስለ ተገለጠ ስለ ልጁ ነው፤ እርሱም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።” ጳውሎስ እዚህ ላይ ክርስቶስ ከዳዊት ዘር እንደሆነ ይነግረናል ። ፊልጵስዩስ 2:6_8 እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቈጠረውም፥ ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ፥ በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ፥ ለሞትም ይኸውም የመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ሆነ። *የመለኮት ሙላት የተገለጠው በክርስቶስ ነው ሰው ሆኖ ቢመላለስም ሙሉ መለኮታዊ ባህሪውን አምላክነቱን ይዞ ነው። እግዚአብሔር ወልድ ለምን ሰው ሆነ?? -በአንድ አዳም ሞት ወደ አለም እንደገባ ህይወት ደሞ በእየሱስ እንዲሆንልን።( ሮሜ 5:12_20) -ሞትንና ሰይጣንን እንዲያሸንፍልን ነው:: (ዕብራውያን 2:14)